የበለጸጉ የምዕራብ አገሮች የኢኮኖሚን ጫና እና አሰራር ለመቋቋም ታስቦ የተመሰረተው ብሪክስ፤ ስሙን የወሰደው ከመጀመሪያዎቹ መስራች አገሮች ብራዚል፣ ሩስያ፣ ህንድ ቻይና እና ደቡብ አፍሪካ የእንግሊዝኛ ስሞቻቸው (BRICS) የመጀመሪያ አልፋቤቶችን በመውሰድ ነው።
ኢትዮጵያ እንደ አንድ ታዳጊ ሃገር የብሪክስ ማዕቀፍን መቀላቀሏ ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅና የኢኮኖሚ ትብብሯን ለማስፋት እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የባለ ብዙ ወገን ጥናትና ምርምር ዳ/ጄ ከፍተኛ ተመራማሪ ሀይማኖት እሸቱ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ተመራማሪዋ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ብሪክስን በአባልነት ለመቀላቀል ያቀረበችው ጥያቄ እንደ ትልቅ የድፕሎማሲ ድል የሚቆጠር ሲሆን ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በማስገኘቱ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመው ያላትን የወደፊት አቅም እና ተስፋ በማሳየት፤ ታሪኳን በማጉላት የመሪዎች ጫናም ተጨምሮበት ብሪክስን ልትቀላቀል ችላለች ብለዋል፡፡
በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሰሚነት ከማሳደግ በላይ የተለያዩ የመሠረተ-ልማት ፕሮጀክቶቿ በቡድኑ የልማት ባንክ በኩል ፋይናንስ እንዲያገኙ በር ይከፍታል፡፡ በብሪክስ አባል አገራት መካከል የሚኖረው የንግድ፣ የኢንቨስትመንት፣የባህል እና የፖለቲካ ቁርኝት የላቀ ደረጃ ላይ ለመድረስ፤ ኢትዮጵያ የዚህ ስብስብ አባል መሆኗ ዲፕሎማሲያዊ ተፅዕኖዋን የበለጠ የሚያሳድግ እንደሚሆን አስገንዝበዋል፡፡
ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ከምዕራባውያን ጋር ያላትን ወዳጅነት ያሻክረው ይሆን ብለን ለጠየቅናቸው ተመራማሪዋ ሲብራሩ “ኢትዮጵያ እንደመርህ የምትከተለው አንዱን ለመግፋት ሌላኛውን ደግሞ ለመደገፍ” አለመሆኑን አንስተው ከሁሉም ጋር ተቀራርቦ መስራትን እንደምትፈልግ፤ መሰረት የምታደርገውና የምትቆመው ከብሄራዊ ጥቅሟ አንጻር መሆኑን አመላክተዋል፡፡ከምዕራባዊያን ርቃ ከብሪክስ ወይም ደግሞ ከምስራቁ እና ከደቡብ ለደቡብ ለመወገን ሳይሆን አማራጯን ለማስፋት ነው፡፡ ምክንያቱም ከምዕራብያውያን ጋርም የምትጋራቸው ብዙ ትብብሮች መኖራቸውን አንስተዋል ፡፡
