በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የባለ ብዙ ወገን ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር ጀኔራል ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር እልፍነሽ ሙለታ እንደገለጹት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙን በውጤታማነት መተግበሩ ለኢኮኖሚክ ድፕሎማሲው ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው አመላክተዋል፡፡
ድፕሎማሲው በኢኮኖሚው ላይ ወሳኝ ሚና እንዲኖረው ለማድረግ የጥናትና ምርምር ተቋማት የተለያዩ ኮንፈረሶችን ማድረግ፣ፖሊሲ ብሪፊንግ መስራት እና ከፖሊሲ አውጭዎች ጎን በመሆን ምክረ ሃሳብ ማቅረብ ይገባል ብለዋል፡፡ በተለይ የውጭ ኢንቨስተሮች ወደ ሃገራችን ገብተው በነጻ ገበያው እንዲሳተፉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን አጠናክሮ ማስቀጠል ለማክሮ ኢኮኖሚው እንቅስቃሴ አስፈላጊ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡ ተቋሙ የጥናትና ምርምር ተቋም ስለሆነ በሪፎርሙ ላይ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ዶ/ር እልፍነሽ አክለውም እንደገለጹት መንግስት በቅርቡ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም መተግበሩ በግሉ ዘርፍ ለሚመራ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ መሰረት እንደሚሆን ጠቁመው የተለያዩ ሀገራዊ ፋይዳዎች እንደመኖሩትም ገልጸዋል፡፡ ለአብነትም በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመንን ለማረጋገጥ፣ በአቅርቦት እና በፍላጎት መካከል ያለውን የውጭ ምንዛሪ መዛባት ለማስተካከል፣ በንግድ ግብይቱ በወለድ ተመን ላይ የተመሠረተ የገንዘብ ፖሊሲ ሥርዓት ለመፍጠር እንዲሁም የፊስካል ፖሊሲ ማሻሻያችን የመንግሥት ፋይናንስ ጫናዎችን እንዲቀንሱ የሚያግዝ መሆኑን እና በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት፣ በዓለም ባንክ እና በሌሎች ወሳኝ የልማት አጋሮቻችን የሚደገፈው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራማችን ለሀገራችን ኢኮኖሚ በርካታ ጥቅሞችን እና ውጤቶችን እንደሚያስገኝ አብራርተዋል፡፡ በተያያዘም የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙን ከሀገር በቀል ኢኮኖሚው ጋር አጣምሮ መስራቱ ገበያ መር ኢኮኖሚው ውጤታማ እንደሚሆን ያደርገዋል ብለዋል ፡፡
የማሻሻያውን ሂደት ተከትሎ ተጋላጭ የኅብረተሰብ ከፍሎች በሪፎርሙ እንዳይጎዱ የተለያዩ ድጎማዎችን እያደረገ መሆኑን ጠቁመው በኢኮኖሚው ውስጥ ሊከሠት የሚችለውን የመልካም አስተዳደር ብልሹነት እና ሕገ-ወጥነትን ለመከላከል መንግሥት በህገ-ወጥ ነጋዴው ላይ የነቃ ቁጥጥር በማድረግ እርምጃ መውሰዱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በገለጻቸው አንስተዋል፡፡