በኢትየጵያና በግብጽ ዋነኛው የግንኙነት መስክ እየወሰነ ያለው የደንበር ተሻጋሪ ውሃ መሆኑ ተመላከተ፡፡
መስከረም 15 ቀን 2017 ዓ.ም በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ጉዳዮች ጥናትና ምርምር ዳይሬክተር ጀኔራል ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ሄኖክ ጌታቸው በኢትየጵያና በግብጽ ዋነኛው የግንኙነት መስክ እየወሰነ ያለው ጉዳይ የአባይ ደንበር ተሻጋሪ ውሃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በገለጻቸው እንዳብራሩት ኢትዮጵያ የአባይን ደንበር ተሻጋሪ ውሃ በፍትሃዊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ለመጠቀም ከምታደርጋቸው ጥረቶች የህዳሴ ግድብን በመገንባት የኢትዮጵያውያንን የመልማትና የማደግ ጥያቄዎችን መመለስ መሆኑንና ይህንንም እንቅስቃሴ አጠናክራ እነደምትቀጥል አብራርተዋል፡፡
በሌላ በኩል ግብጽ ፍትሃዊ አጠቃቀምን እንደማትደግፍና የ1929 እና 1959 ውል እንዲተገበርላት የምትፈልግ ሃገር መሆኗን ጠቁመዋል፡፡ ይህ ውል የቅኝ ግዛት ውል መሆኑን ደግሞ ኢትዮጵያ እና የላይኛው ተፋሰስ ሃገራት እንደማይደግፍ አስገንዝበው ግብጽ በአፍሪካ ቀንድ ላይ የምትከተለው ዋነኛ ፖሊሲዋ ኢትዮጵያ በአባይ የውሃ ተፋሰስ ለመልማት የምታደርገውን ጥረት ማደናቀፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዚህም የተነሳ ግብጽ ከዲፕሎማሲ ባሻገር ወታደራዊ ግንኙነቶች ከጎረቤት አገሮች ጋር ማድረግ፣የኢኮኖሚ ጥረቶች ላይ ተጽኖዎችን ማሳደር ከፋይናሽያል ተቋማት ጋር ያላትን የግንኙነት መረቦች ማስፋት ነው፡፡ በተጨማሪም ኢትዮጵያና ሶማሊያ የገቡበትን የድፕሎማሲ ውጥረት ተገን በማድረግ ከሶማሊያ ጋር ያላትን ግንኙነት ማጠናከር መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ዶ/ር ሄኖክ አክለውም እንደገለጹት በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት ለዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር ስትወዛገብ የነበረችው ግብጽ ኢትዮጰያን ከመክበብ ስትራቴጂ ከምትከተላቻው አንዱ ከሶማሊያ ጋር የወታደራዊ ትብብር ስምምነት መፈራረሟ ኢትዮጵያን እንዲሁም የአፍሪካን ቀንድ ቀጣናን ስጋት ላይ የሚጥል ነውም ብለዋል፡፡ በተጨማሪም የተለያዩ የሶማሊ ክልሎችም በብዛት ሶማሊያ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ግዛቶች ጉዳዩ እያሳሰባቸው እንደመጣ ስጋታቸውን አመላክተው ይህ እንቅስቃሴ እየቀጠለ ከሄደ በሃገራቱ መካከል ውጥረት እጨመረ እንደሚሄድ የራሱ የሆነ የደህንነት ስጋት የመፍጠር አዝማሚያ ሊጨምር ይችላልም ነው ያሉት ፡፡ በሌላ በኩል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ይህ ሁኔታ እንደዚህ መቀጠሉ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ የደህንነት ስጋት የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አስገንዝበዋል፡፡
ኢትዮጵያ ላይ ያሉ ስጋቶችን ለመቅረፍ በየሃገራቱ ድፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን ማጠናከር፣ ከሶማሊያ ጋር ያሉ ውጥረቶችንም ባሉት ድፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች እና በቱርክ አሸማጋይነት እተሄደ ያሉ ጥረቶችን አጠናክሮ በማስቀጥል ስጋቶችን መቀነስ እንደሚገባ ምክረሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡