የመከላከያ ድፕሎማሲ ወታደራዊ ግንኙነቶችን በማጎልበት፣ የጸጥታ ትብብርን በማሳደግ፣የሰላም ማስከበር ጥረቶችን በማጎልበት እና አለም አቀፍ አጋርነቶችን በማጠናከር ለውጭ ጉዳ ፖሊሲ ወሳኝ ሚና ይጫወታል:: የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር የተከበሩ አቶ ጃፋር በድሩ

የካቲት 27 ቀን 2016 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ኢንሰቲትዩት እና በኢፌድሪ የመከላከያ ሚኒስቴር የውጭ ግንኙነትና ወታደራዊ ትብብር ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት መከላከያ ድፕሎማሲ ፖሊሲ ለኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ግቦች ማስፈጸሚያ ስትራቴጅ፣ ተሞክሮዎች፣ እድሎች እና ተግዳሮቶች በሚል ርዕስ የፖሊሲ ምክክር መድረክ የመከላከያ ከፍተኛ መኮንነች እና የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ድፕሎማቶች በተገኙበት በኢንስቲትዩቱ አዳራሽ ተካሄደ፡፡
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር የተከበሩ አቶ ጃፋር በድሩ በመክፈቻ ንግግራቸው እንደገለጹት መንግስታት ሃገራዊ ጥቅሞቻቸውን ለማስጠበቅ የመከላከያ ድፕሎማሲ አንዱ መሆኑን ጠቁመው አሁን ላይ በድፕሎማሲው መስክ ከፖለቲካ በተጨማሪ በማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና በወቅታዊ ጉዳዮች ትኩረት አድርጎ መወያየት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የመከላከያ ድፕሎማሲ ወታደራዊ ግንኙነቱን ለማጎልበት፣ የጸጥታ ትብብርን ለማሳደግና የሰላም ማስከበር ጥረቶችን በማጠናከር ዓለማቀፋዊ ግንኙነቶችን ማሳደግ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡
የመከላከያ ሰራዊት ሰላም ማስከበር ዋና ሃላፊ ሜጀር ጀነራል አዳምነህ መንግስቱ በበኩላቸው ጀግኖች አባቶቻችን ሃገራችን በቅኝ ግዛት ሳትያዝ ያስረከቡንን ይህችን ትልቅ ሃገር ሉዓለዊነቷን በማስከበር ሰፊ ስራዎችን እየተሰሩ መሆኑን ገልጸው የዛሬው የምክክር መድረክም መከላከያ ድፕሎማሲያችንን የሚያጠነክር ወሳኝ አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡
በምክክር መድረኩ የመከላከያ ድፕሎማሲ ምንነትና አስፈላጊነት፣ በአፍሪካ ቀንድ ቀጠናዊ ደህንነት መረጋጋት በማስፈን ረገድ የኢ.ፌ.ድ.ሪ መከላከያ ድፕሎማሲ እና ኢትዮጵያ ከታላላቅ ሃገሮች ጋር ያላት ግንኙነት ለማጠናከር የመከላከያ ድፕሎማሲ አስተዋጽኦ በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *