የኢትዮጵያን የ115 ዓመታት የውጭ ግንኙነት ትኩረቶችን የሚያስቃኝ መጽሐፍ ተመረቀ
ጥር 3/2016 (አዲስ ዋልታ) የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከ1901 እስከ 2016 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎችን የሚያስቃኝ መጽሐፍ አስመርቋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር በመተባበር ያዘጋጁት የፓናል ውይይት “ዲፕሎማሲያችን ለብሔራዊ ጥቅማችን” በሚል መሪ ቃል በሳይንስ ሙዚዬም እየተካሄደ ሲሆን በመድረኩ የኢትየጵያን የ115 ዓመታት የውጭ ግንኙነት ትኩረቶችን እና ዲፕሎማሲ ጉዞ የሚያሳይ መጽሐፍ ተመርቋል፡፡
በዚህ የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ ሳምንት አካል በሆነው መድረክ ላይ የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ የምታደርገውን የዲፕሎማሲ ስራ አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጉዞ በመንግስታት ቅብብሎሽ ውስጥ ተጠናክሮ መቀጠል የቻለ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
መድረኩ ያለፈውን ጉዞ ለማጤን እና ለቀጣይ የሚጠቅሙ ግብአቶች የሚገኙበት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
በመድረኩ የመነሻ ሀሳቦች ቀርበው ውይይት እየካሄደ ሲሆን ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ አምባሳደሮች፣ የውጭ ሀገራት አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች እየተሳተፉ እንደሚገኙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡