ውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት 18ኛውን የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓልን  አከበረ።

ህዳር 27 ቀን 2016 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት  ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት ጋራ  በጋራ በመሆን  18ኛውን የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን “ብዙሃነት እና እኩልነት ለሃገራዊ አንድነት ” በሚል መሪ ቃል   አክብረዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምኒስትር ዴኤታ  ክብርት አምባሳደር ብርቱካን አያኖ  በዓሉን አስመልክቶ  መርሃ ግብሩን በንግግር በከፈቱበት ወቅት  በኢትዮጵያ የታሪክ ማህደር ውስጥ፣ ለብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለዘመናት የእኩልነትና የማንነት ጥያቄ ዋስትና የሰጠ እና ሕገ መንግሥቱ የፀደቀበት ህዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም አንድ ታሪካዊ ቀን ተደርጎ መጻፉን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ህገ መንግስታዊ መብት የተረጋገጠበት ዕለት እንደ መሆኑ በሃገር አቀፍ ደረጃ እንዲሁም በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ዲፕሎማሲዎች እና ቆንጽላዎች  በዓሉን  በድምቀት እያከበሩ መሆኑን አሳውቀዋል።
ክብርት አምባሳደር አክለውም ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን እንዲጎለብት  በመቻቻልና  በመከባበር  ቀደምት አባቶቻችን  ያቆዩልንን ሀገር  ለተተኪው ትውልድ በፍቅር  በማስረከብ ለብዙሃነትና እኩልነት መከበር የበኩላችን ሃላፊነት መወጣት አስፈላጊ መሆኑን ገልጸው ለዚህም የዲፕሎማሲ ሥራችንን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የዕለቱን የመወያያ ጽሁፍ  በውጭ ጉዳይ ሚኒስተር  የአቅም ግንባታ አማካሪ  አቶ ወንድሙ ገዛኸኝ  ‘’ሕብረ ብሄራዊ ፌደራላዊ ሥርዓት እና የሠላም ግንባታ በኢትዮጵያ’’ በሚል ርዕሰ የቀረበ ሲሆን   ለአብነትም የፌደራሊዝም ትርጉም፣ የፌደራል ስርዓት ዋና ዋና ዓላማዎች ፣ የፌደሬሽን ዓይነቶች፣ ብሔር እና ብሔርተኝነት የሚሉትን  የመወያያ ነጥቦች በዝርዝር አቅርበው  ውይይት ተደርጎባቸዋል።
በመጨረሻም በውይይቱ  አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበው ጉዳዩ በሚመለከተው የስራ ሃላፊ አቶ  ወንድሙ   ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቶ በዓሉ ተጠናቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *