አዲስ አበባ ፤ ህዳር 26/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀል ለባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ማደግና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ሚናው የላቀ መሆኑን በውጭ ጉዳይ ኢኒስቲትዩት የባለብዙ ወገን ድርጅቶች ከፍተኛ ተመራማሪ ተስፋዬ ቦዬሳ ተናገሩ።

ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል አገር መሆኗ የሚኖረውን ጠቀሜታና አጠቃላይ ሀገራዊ ፋይዳውን በተመለከተ ኢዜአ ከኢኒስቲትዩቱ ከፍተኛ ባለሙያ ጋር ቆይታ አደርጓል።

በውጭ ጉዳይ ኢኒስቲትዩት የባለብዙ ወገን ድርጅቶች ከፍተኛ ተመራማሪ ተስፋዬ ቦዬሳ፤ ኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀሏ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት ያስረዳሉ።

ከዚህም መካከል በተለይም በዓለም የዲፕሎማሲ መድረክ ፋይዳው የላቀ መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ለምትከተለው የባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ መጠናከርና የጋራ ተጠቃሚነት ወሳኝ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በዓለም የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ ተሰሚነቷና ተቀባይነቷ እንዲያድግም ብሪክስ የራሱ አስተዋጽኦ አለው ሲሉ አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ፤ ያደረጉት የዲፕሎማሲ ጥረት ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል በመሆን በዲፕሎማሲው ስኬታማ አድርጓታል ብለዋል።

ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጥረቷን በማጠናከር በተለይም በአህጉራዊ መድረኮች አፍሪካን በመወከል የመሪነት ሚናዋን በአግባቡ ለመወጣትና ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ የሚያግዝ መሆኑንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ እና ሌሎችም የብሪክስ አባል የሆኑ አገራት ሰፊ የልማት አቅም ያላቸው በመሆኑ ለጥምረቱ መጠናከር የላቀ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑንንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ብሪክስን መቀላቀል ለባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ ግንኙነት ማደግና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የውጭ ምንዛሬ እጥረትን ለመፍታት ብሪክስ ሌላ አማራጭ መሆኑን ገልጸው ለንግድና ኢንቨስትመንት መሳለጥም ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

በደቡብ አፍሪካ ነሐሴ 2015 ዓ.ም በተካሄደው የብሪክስ 15ኛ መደበኛ ጉባኤ ኢትዮጵያን ጨምሮ አርጀንቲና፣ ግብጽ፣ ኢራን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች የብሪክስ አባልነት ጥያቄያቸው ተቀባይነት ማግኘቱ ይታወቃል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *