የምስራቅ አፍሪካ አገራት ቀጣናዊ ትብብር ዋንኛ የዲፕሎማሲያቸው የትኩረት ማዕከል ማድረግ ይኖርባቸዋል።
አዲስ አበባ፤ ህዳር 8/2016 (ኢዜአ)፦ የምስራቅ አፍሪካ አገራት በቀጣናው ዘላቂ ሰላምና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብ የሚያስችል ቀጣናዊ የትብብር ዲፕሎማሲ ማጠናከር እንዳለባቸው ተመላከተ።
የውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ግዛቸው አስራት፤ ግጭቶችና የፖለቲካ አለመረጋጋት ለቀጣናው አገራት አሁንም ፈተና ሆነው ቀጥለዋል ብለዋል።
የቀጣናው የጂኦ-ፖለቲካዊና ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ከፍተኛ ቢሆንም የሰላም እጦትና አለመረጋጋት የቀጣናው እድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ነው ያነሱት።
ቀጣናዊ ትብብርና ትስስር ለምስራቅ አፍሪካ አገራት እጅጉን አስፈላጊ ነው የሚሉት ዶክተር ግዛቸው ጉዳዩ ዋንኛው የአገራቱ የትኩረት ማዕከል መሆን እንደሚገባው ገልፀዋል።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ-መንግሥታት (ኢጋድ)፣ የአፍሪካ ሕብረትና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለቀጣናዊ ትስስሩ ድጋፍ ማድረግ እንደሚኖርባቸውም ነው ያነሱት።
ቀጣናዊ ትስስሩ ያለ አገራቱ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እውን እንደማይሆን ገልጸው፤ ለትስስሩ እውን መሆን የአባል አገራቱ ቁርጠኝነትና ፍላጎት ሊኖራቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።
የአገራት ትብብርና ምጣኔ ኃብታዊ ውህደት በቀጣናው ላይ ያሉ የፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮችን ለመፍታት ቁልፍ መሆኑንም ነው ዶክተር ግዛቸው የገለጹት።
አገራት ሽብርተኝነት፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ኮንትሮባንድና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ቀጣናዊ የአሠራር ማዕቀፎችን መዘርጋትና ያሉትንም ማጠናከር እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል።
ለዚህም አገራት ከሚያከናውኑት ሥራ ጋር የሚጣጣም የፖሊሲ ማዕቀፍ ሊኖራቸው እንደሚገባና መንግሥታትም ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በቁርጠኝነት መሥራት እንዳለባቸው ገልፀዋል።